የአርሴናል አስደንጋጭ አቋም መዋዠቅ አሁንም ቀጥሏል። በብራይተን አሜክስ ስታድየም 2-1 ተሸንፏል።

የክሪስ ሂውተን ቡድን ጨዋታውን በከፍተኛ ፍጥነት ነው የጀመሩት። ፈጥነው ባደረጉት የተደጋጋሚ ማጥቃት አርሴናልን በጊዜ አምበርክከዋል።

ከሁለቱ ቡድኖች የተራበ የሚመስለው ብራይተን ነበር። አርሴናሎችን ኳሱ ላይ ፋታ አልሰጧቸውም። አርሴናል ኳሱን ሲይዝ በከፍተኛ ጫና ይጫወታሉ። እንሱ ኳሱን ስይዙት ፈጥነው ያጠቃሉ። ገና በ25ኛው ደቂቃ በሁለት ግሎች መምራት ችለዋል።

የመጀመርያውን ከኮርና የተሻገረ ኳስ ፒተር ቼክ በሰራው ጥፋት ኳሷ ሊዊስ ደንክ እግር ስር ወደቀች። አገባ።

እንደገና ፓስካል ግሮስ ለኖካርት አቀብሎ የሞከረው ኳስ በፒተር ቼክ ዳነች። ግን ግሮስ አላበቃም። አሻግሮ የላካት ኳስ በግሌን መሪ ጭንቅላት ተገጭታ ገባች። ጎሉ የመሪ የአመቱ 11 ጎሉ ሁና ተመዝግባለች። ፒተር ቼክ ሁለተኛውንም ጎል ማዳን ይችል ነበር።

የአርሴናሉ ተከላካይ ካለም ቼምበርስ የብራይተኑን ጆሴ ኢዝቂዌርዶን ፍጥነት መቋቋም አልቻለም ነበር። ኢዝቂዌርዶ በሚፈጥራቸው እድሎች ብራይተን በተደጋጋሚ እድል መፍጠር ችለው ነበር።

ጨዋታው እረፍት ሲደርስ ፒዬር ኤምሪክ ኦባምያንግ ከቅርብ ያገባው ኳስ ለአርሴናል አንድ ጎል መልሷል።

አርሴናል በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለው ነበር። ግን ከድሮው አቋማቸው አንጻር በጣም ገና ናቸው። እኩል የምታደርጋቸውን ጎል ማግኘት አልቻሉም።

ብሪይተኖች ምርጥ 10 ውስጥ ይጨርሳሉ።

የጨዋታው 5 መነጋገርያ ነጥቦች።

1) የግሌን መሪ ማንሰራራት

34 አመቱ ነው። ግን ግሌን መሪ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በፕሪምየር ሊጉ የተመቸው ይመስላል።

አርፍዶ ነው የበሰለው። ድሮ ለክሪስታል ፓላስ እና ቦርንመዝ ይጫወት የነበረው አጥቂ ብራይተንን ቤቱ አድርጓል። ከየትኛውም ቡድን ጋር ሲጫወት አስፈሪ ነው።

በጨዋታው ያገባው ጎል በ2018 6ኛ ጎሉ ናት። በ2018 ከሱ በላይ ማግባት የቻሉት ሞ ሳላ እና ሰርጂዎ አግዌሮ ብቻ ናቸው።

ፍጥነት ያለው ተጨዋች አይደለም። የእግር ኳስ ብስለቱ ግን ከሚገመተው በላይ ነው።

በአየር ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አርሴናሎች መቋቋም አቅቷቸው ነው ያረፈዱት።

2) ኦባምያንግ አሳማኝ አልነበረም

ኦባምያንግ በዶርትመንድ ከክንፈኛ ወደ ጨራሽ አጥቂ የተቀየረበት ጊዜ ነው። ጀርመን እያለ ካገባቸው 141 ጎሎች አንዱ ብቻ ነው ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ የነበረው።

አርሴናል አስቸጋር ጊዜ ላይ ነው የመጣው። ቢሆንም የጋቦኑ ተጨዋች አሳማኝ እንቅስቃሴ ለቡድኑ እስካሁን ማድረግ አልቻለም።

ከዚህ ጨዋታ በፊት ብቸኛው ጎሉ ከኤቨርተን ጋር ያገባው ነበር። በትላንት ጨዋታ ማግባት ቢችልም ለአብዛኛው ደቂቃ ዝም ብሎ ተሰላፊ ነበር። በጨዋታው ውስጥ መግባት ተስኖት ነው ያረፈደው።

የአርሴናል ደጋፊዎች ከአጥቂያቸው የተሻለ ይጠብቃሉ።

3) የቼክ ጊዜ አብቅቶ ይሆን

ፒተር ቼክ በፕሪምየር ሊግ ታሪክ ምርጥ ጠባቂዎች ውስጥ አንዱ ነው። 3 ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸንፏል።

ቬንገር አርሴናልን ከለቀቀ ግን ቼክ አብሮት ይከተለዋል ይባላል።

ጠባቂው በዚህ አመት 36ኛ አመቱን ያከብራል። በ16አመት ታሪኩ ውስጥ እንደዘንድሮ የወረደ አቋም ኑሮት አያውቅም። ፍጥነቱ ቀንሷል።

ለገቡት ሁለቱም ጎሎች ተጠያቂ ነበር።

4) የብራይተን አጥቂ መስመር

አሰልጣኙ በብራይተን ትልቅ ስራ ሰርቷል። ከጀርባ ጀምሮ እስከ ፊት ድረስ የተሟላ ቡድን ነው። በላፉት 6 ጨዋታዎች ግን የአጥቂ መስመራቸው ልዩ ሆኗል።

5) ቬንገር ይውጣ

ቬንገር በተቀመጠበት እንደተለመደው እየቆዘመ ነበር። መሬት መሬት እያየ ንዴት ይነበብበት ነበር።

ለአርሴናል ከባድ ግዜ ነው አሁን። ቡድኑ ተስፋ የቆርጠ ይመስላል። ነገሮች እየሰሩለት አይደለም። ከተጨዋቾቹ በሲቲ ያስተናገዱትን ሽንፈት የሚያስረሳ እንቅስቅሴ ጠብቆ ነበር። አልሆነም።

አሁን የሚጠየቀው ጥያቋ ቬንገር ይወጣል ወይ ሳይሆን መቼ ነው የሚወጣው ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here