ክርስታያኖ ሮናልዶ ለሪያል ማድሪድ ያገባው ሁለት ጎል ቡድኑ አይባርን 2-1 እንዲያሸንፍ ረድቶታል። ሁለተኛ ከተቀመጡት አትሌቲኮ የነጥብ ርቀቱን ወደ 4 አጥበዋል።

የሉካ ሞድሪችን ግሩም ኳስ ተቆጣጥሮ በ34ኛው ደቂቃ ሮናልዶ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ኳስ አግብቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ የአይባሩ ኢቫን ራሚስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። በ84ኛው ደቂቃ ከዳኒ ካርቫሃል የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ አግብቶ ሮናልዶ ማድሪድን አሸናፊ አድርጓል።

ማድሪድ ከመሪዎቹ ባርሴሎና አሁንም በ12 ነጥብ ርቀው ተቀምጠዋል። የአመቱ አጀማመራቸው አመርቂ ባይሆንም ወደ መጨረሻው ማድሪዶች ተጠናክረዋል።

የጨዋታው 5 መነጋገርያ ነጥቦች።

1) ሮናልዶ ሜሲ ላይ እየደረሰ ነው

ሊዮኔል ልጁ በመወለዱ ምክንያት ቡድኑ ከማላጋ ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ አይሰለፍም። ሮናልዶ እድሉን ተጠቅሞ ከሜሲ ጋር ያለውን የጎል ልዩነት ወደ 6 ቀንሶታል።

ሮናልዶ 18 ጎሎች አሉት። ሜሲ 24። በማሃላቸው ሉዊስ ስዋሬዝ በ20 ጎል ሁለተኛ ነው።

ሮናልዶ በመጀመርያው 8 ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ነው ማግባት የቻለው። በዛ ግዜ ሜሲ ከፍተኛ ቀዳሚነት ተቆናጧል።

ግን እንደሁልግዜ ሮናልዶ ከኋላ ተመልሶ ጎል የማግባት ችሎታውን ማሳየት ችሏል። በመጨረሻዎቹ 7 ጨዋታዎች 13 ጎሎች አሉት።

2) ሞድሪች የጨዋታው አቀጣጣይ

ማድሪድ በ ላሊጋው የሚጫወትለት ነገር አለመኖሩ ቀሪ ጨዋታቸው ደባሪ ይሆናል ተብሎ እንዲታሰብ አድርጎታል።

የዛሬው ጨዋታ እድሜ ለሞድሪች ምንም ደባሪ እንዳይባል አድርጎታል። የአይባር ስታድየም ሞድሪች ዛሬ ያሳየውን አይነት እንቅስቃሴ አይቶ አያውቅም ለማለት ያስደፍራል።

የዛሬው ጨዋታ ሞድሪች ከጉዳት የተመለሰበት ነበር። ማድሪድ በሜዳው ፒኤስጂን ካሸንፈበት ጨዋታ ጀምሮ ሞድሪች በጉዳት ከሜዳ ርቋል።

ሞድሪች የማድሪድን ቀዳሚነት ጎል ለሮናልዶ ባቀበለው ኳስ ፈጥሯል። እራሱም ለማግባት ተቃርቦ ነበር።

ሙሉ ጨዋታ የሚያቀብላቸው ኳሶች ልዩ ነበሩ።

3) ራሚስ ራሞስን በልጦታል

ሰርጂዎ ራሞስ የአይባሩን አጥቂ ኢቫን ራሚስ በሁሉ ነገር ይበልጠዋል። በሚጫወትበት ቡድን፣ ባሸነፋቸው ውድድሮች፣ ባለው የሜዳል ዝርዝር ወዘተ።

በዛሬው ጨዋታ ግን የማድሪዱ ተከላካይ ራሚስ ጫፍ መድረስ አልቻለም። ሙሉ ጨዋታ ጥላ ሲያሳድድ ነበር።

የራሚስ ብልጠት የተሞላበት እንቅስቃሴ ራሞስን ከብዶት አርፍዷል። የቡድኑንም ብቸኛ ጎል ያገባው እሱ ነው። ቡድኑ ግን ውጤቱን አስጠብቆ መውጣት አልቻለም።

4) ቤል ችግር አለመሆኑን አሳይቷል

አርብ የወጡ ዘገባዎች ጋሬዝ ቤል ለዚዳን እራስ ምታት እንደሆነበት ሲዘግቡ ነበር።

ዚዳን ስለሱ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ስለ ቤል ሲጠየቅ ምቾት አይሰማውም። በተደጋጋሚ ስለሱ ስለሚጠየቅ ይሆናል።

በሁለቱም የፒኤስጂ ጨዋታዎች ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው ቤል በዛሬ ጨዋታ እድል ተሰቶታል። አሰልጣኙን አላሳዘነም በዛሬ ጨዋታ።

ለሮናልዶ ጥሩ እድል መፍጠር ችሏል። ለራሱም ጥሩ ሙከራዎችም ሲያደርግ ነው ያረፈደው።

5) ማድሪዶች ማድሪድን እየመሰሉ ነው

ማድሪድ ባለፈው አመት ዋንጫውን የበላው ቡድን ለመሆን ተቃርቧል። ውጤቶች እያስመዘገቡ ነው። በዚህ አመት እስካሁን ባርሴሎና የሚጫወተውን አይነት የሚፈስ እግር ኳስ መጫወት አልቻሉም። ቢሆንም ጥሩ ተንቀሳቅሰው ወደ ማሸነፍ ተመልሰዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here