ፊሊፔ ኩቲንሆ በእግሩ ጀርባ ያገባት ኳስ ቡድኑ ባርሴሎና ማላጋን አሸንፍፎ የ11 ነጥብ ከፍተት እንዲፈጥር አግዟል።

ሚስቱ 3ኛ ልጁን የወለደችለት ሜሲ በጨዋታው አልተሰለፈም። የጨዋታውን መጀመርያ ጎል ሉዊስ ስዋሬዝ ከጆርዲ አልባ የተላከለትን ግሩም ኳስ በጭንቅላቱ አግብቷል።

ኩቲንሆ ሁለተኛውን ጎል ዴምቤሌ በመሬት የላከለትን ኳስ በጀርባ እግሩ ግጭቶ አግብቷል። የማላጋው ተጨዋች ሳሙ ጋርሲያ ጆርዲ አልባ ላይ በሰራው ጥፋት ቀይ አይቷል።

ማላጋ አንድ ጎል መመለስ የሚችሉበትን እድል አምክነዋል። ዩሰፍ ኤን ኔሲሪ በጭንቅላት የገጫት ኳስ ወታበታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ባርሴሎና ተቀዛቅዘው ነው የተጫወቱት። በሳምንቱ ከቼልሲ ጋር በሚያደርጉት ፍልሚያ ሃይል ለመቆጠብ ይመስላል።

የጨዋታው 5 መነጋገርያ ነጥቦች

1) የባለፈው አመት ችግሮች ተቀርፈዋል

ይህን ጨዋታ አይቶ መገመት ባይቻልም ባርሴሎናን ማሸነፍ የቻለው የመጨረሻ ቡድን ማላጋ ነው። በኤፕሪል 2017 ባደረጉት ጨዋታ ማላጋ 2-0 አሸንፈዋል። ከዛ ቀን ጀምሮ ባርሴሎና በ35 ጨዋታ አልተሸነፈም።

ማላጋ ከዛ ጨዋታ ጀምሮ ብዙ ተጨዋቾቻቸውን አተዋል። ሁለቱንም ጎል አግቢዎቻቸውን አተዋል። = ምርጥ ብቃቱን ባርሴሎና ላይ የሚያሳየው በረኛቸው ካርሎስ ካሜኒም የለም። የሱ ተተኪ ሮቤርቶ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቷል። ባርሴሎናን ማቆም ግን አልቻለም።

2) ዴምቤሌ ጥሩ ተጫውቷል

ጉዳትና አቋም መዋዠቅ የተጠናወተው ዴምቤሌ በደጋፊዎችና በሚዲያ ሲተች ከርሟል።

ቡድኑ ከኤስፓንዮል ጋር ባደረገው የካታላን ሱፐር ካፕ ጨዋታ እንቅስቃሴው በጣም የወረደ ነበር። በዚህ ጨዋታ ባገኘው እድል ጥሩ መንቀሳቀስ ነበረበት።

እሱንም አሳክቷል። ክለቡ ለምን ከፍተኛ ሂሳብ አውጥቶ እንደገዛው አሳይቷል።

ለኩቲንሆ ጎል አመቻችቶ ያቀበለው እሱ ነው።

3) ሜሲ ለቼልሲ ጨዋታ እረፍት አግኝቷል

ከጨዋታው በፊት ትልቁ ዜና ሜሲ ፍቅረኛው አንቶኔላ ሮኩዞ ልጃቸውን ስትወልድ አብሯት ለመሆን ብሎ በጨዋታው እንደማይጀመር ነበር።

ያለ ሜሲ ባርሳዎች ደህና ነበሩ። የቼልሲ ደጋፊዎች ግን የልጁን ውልደት እንዲራዘም ቢመኙ አይፈረድባቸውም።

4) ማቆም ያማይቻለው ሱዋሬዝ

ሱዋሬዝ ትላንት ባገባው ጎል በላሊጋ ካሉ ሁሉም ቡድኖች ላይ አግብቷል ማለት ነው። ማላጋ ብቻ ነበር የቀረው።

ጎሉ ቀላል ነበር። የጆርዲ አልባ ግሩም ኳስ ያለቀለት ኳስ ነበር። ሜሲ የሚያቀብለው አይነት ኳስ ነበር።

የስዋሬዝ ቦታ አጠቃቀም አስገራሚ ነበር። ከሜሲ ቀጥሎ ለተከላካዮች ቅዠት የሆነው የባርሴሎና ተጨዋች እሱ ነው።

በዘንድሮ ውድድር አመት በላሊጋ እስካሁን 21 ጎሎች አሉት። የቡድን አጋሩ ሜሲ 24 አለው።

5) ማላጋ መውረጃ ቀጠና ውስጥ

ማላጋ ከመውረጃው ቀጠና ለመውጣት 7 ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። በጨዋታው ታግለው ተጫውተዋል። ንዴታቸውን ግን መደበቅ አልቻሉም።

ሳሜ ጋርሲያ ጆርዲ አልባ ላይ የፈጸመው ጥፋት ተጨዋች በአጭሩ ማስቀረት የሚችል አይነት ጥፋት ነበር። የማላጋ ተጨዋች ቀይ ሲያይ በውድድር አመቱ ለ8ኛ ግዜ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here